- የመሬት ማስተካከል ሥራው በሚሠራበት ወቅት መጠኑ ያልታወቀ ፈንጅ በመጠቀም ከፍተኛ ፍንዳታ እንዲከሰት በመደረጉ ከ100 በላይ ቤቶች ጣሪያቸው ሲጎዳ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ይናገራሉ፡፡
- የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው ዝርዝር ጥናት ያልተደረገባቸውና የተዘጋጀ መሪ እቅድና ዲዛይን የላቸውም
- አዋሽ ፓርክ አካባቢ ቅድመ ጥንቃቄ ባለመደረጉ የዱር አራዊቶቹ ፓርኩን ጥለው ኮብልለዋል
የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትሎ የመጣው የባቡር ትራንስፖርት ለበርካታ አገሮች ከስልጣኔ ማማ ላይ መቀመጥ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ለአብነትም እንግሊዝን ኃያል እንድትሆን ካደረጓት ነገሮች መካከል አንዱ የባቡር መስመር ቴክኖሎጅን በሁሉም ግዛቶቿ በመገንባት የትራንስፖርት ዘርፏን በተቀላጠፈ መልኩ ማስኬድ መቻሏ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
ባቡር ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል ግንኙነትን በተሳለጠ መልኩ በማስኬድና ርቀትን በመስበር አንድ ማህበረሰብ መፍጠር አንዱ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር የግብርና ምርቶችን በተለይ በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተትና እንስሳት ተዋጽኦዎችን በፍጥነት በማጓጓዝ ለገበያ ለማቅረብ የሚረዳ የትራንስፖርት ዘርፍም ነው፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ ጀምሮ ምርቶችን በቀላሉ ተደራሽ እስከማድረግ ድረስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ኢትዮጵያ የባቡር መሰረተ ልማትን ለማስገንባት ብዙም ባትዘገይም በ1890ዎቹ በፈረንሳይ መንግሥት የተገነባው ሸመንደፈር ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱና ዘላቂነቱ ሳይታሰብ በመገንባቱ አገልግሎቱ ለዘመናት መጽናት አልቻለም። በመሆኑም ከ100 ዓመታት ታሪክ በኋላ አዲስ የባቡር መሰረተ ልማት ሊሠራ ግድ ብሏል።
ከዚህም በመነሳት በርካታ የከተማና አገር አቋራጭ የባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተነድፈው እየተተገበሩ ነው። ከእነዚህም አንዱ በአዲስ መልክ እየተገነባ ያለው የአዲስ አበባ ጅቡቲ መስመር ነው። ይህ ፕሮጄክት የዘመኑ ቴክኖሎጂ በሚፈልገው መልኩ ባዲስ መልክ እየተገነባ ይገኝ እንጂ የባቡር መስመሩ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተገቢ የሆነ ዝርዝር እቅድ ሳይዘጋጅለት እንደተገነባ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በዚህም መስመሩ በተዘረጋባቸው አካባቢዎች መተላለፊያ በማጣት በርካታ ሰዎችና ተሽከርካሪዎች እየተቸገሩ መሆኑን በአብነት ይጠቁማሉ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደሚሉት፤ ኮርፖሬሽኑ የሚያካሄዳቸው የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው ዝርዝር ጥናት ያልተደረገባቸውና የተዘጋጀ መሪ እቅድና ዲዛይን ስለሌላቸው ግንባታው ከተከናወነ በኋላ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሳያ ቃሊቲ አካባቢ ከ100 ሜትር በላይ የሚገመት የኮንክሪት ግንባታ በዲዛይን ግድፈት መፍረሱና አዳማ መውጫ አካባቢ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች እንዲያሳልፉበት ታስቦ የተሠራ ማቋረጫ ከፍ ያለ ጭነት የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ አለመቻሉ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
የባቡር መስመሮች በተገቢው ሁኔታ ጥናት ተደርጎባቸው መሠራት ካልቻሉ ለዘመናት መጽናት እንደማይችሉና ለትውልድ ተሻጋሪ ማድረግ እንደማይቻል የሚናገሩት አምባሳደር መስፍን፤ እንደ ገና ላለመመለስ ትኩረት መስጠት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ እንዲሁም የእግረኛና ተሽከርካሪ ማቋረጫ ድልድዮች ዲዛይኑ ውስጥ ተካተው ግንባታው አለመከናወኑ እግረኞችና ተሽከርካሪዎች ላይ መጉላላትን ፈጥሯል ይላሉ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ደቢሶ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ፕሮጀክቶችን ለማሠራት ሲያስብ ዝርዝር እቅድ ሳያዘጋጅ በስምምነቱ መሰረት እንዲሠራ እንጂ ችግሮች ይከሰታሉ በማለት የወደፊቱን እቅድ በማውጣትና በጥናት በመደገፍ ሥራውን ሠርቷል ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንደ እቅድ ያቀረበው ነገር በትራንስፖርት ሚኒስቴር አማራጭ የየብስ ትራንስፖርት ተብሎ የተጠና ጥናትን መሰረት ያደረገ እንጂ የባቡር ፕሮጀክት ግዙፍ እንደመሆኑና ወጪውም ከፍተኛ መሆኑን ከግምት በማስገባት በመረጃ በተደገፈ ሁኔታ ሥራውን አላከናወነም ባይ ናቸው፡፡
ፕሮጀክት ተብሎ ከተሠራ በማንኛውም ወቅት ሊቀርብ የሚችል የራሱ የሆነ ዝርዝር ጥናትና ሰነድ ሊኖረውና ብቻውን መረጃ ሆኖ ሊቀመጥ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ገመቹ፤ በቀጣይ ሥራዎች ላይ ክፍተቶች እንዳይደገሙ ፕሮጀክቶች ጥናትን መሰረት በማድረግ መሠራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በተለይም ፕሮጀክቱ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ስለሚችል ተጽዕኖውን በዝርዝር እቅድ መያዝ አለመቻሉና የአካባቢ ተጽዕኖው ግምገማ ውስጥ አለመካተቱ ትግበራ ላይ ችግር መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ሥራዎች ላይ አተገባበሩ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ አዛሉ ጥላሁን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የአንዳንድ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የተደረገው ግንባታዎች ከተጀመሩ በኋላ መሆኑና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው በተገቢው ሁኔታ ቅድሚያ ባለመሠራቱ በርካታ መስዋዕቶችን እንዲያስከፍል ማድረጉን ይስማማሉ፡፡ በዚህም የመሬት ማስተካከል ሥራው በሚሠራበት ወቅት መጠኑ ያልታወቀ ፈንጅ በመጠቀም ከፍተኛ ፍንዳታ እንዲከሰት በመደረጉ ከ100 በላይ ቤቶች ጣሪያቸው ሲጎዳ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ይናገራሉ፡፡
‹‹በሚተኮሱ ፈንጂዎች አማካኝነት በአዳማ ከተማ ቀበሌ 14 ኮንዶሚኒየም ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ምሰሶዎች እንዲሰነጣጠቁ ሆነዋል›› የሚሉት ወይዘሮ አዛሉ፤ ይህም የሆነው ለአካባቢ ተጽዕኖ ጉዳይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ባለመጠናቱ ነው ይላሉ፡፡
ወይዘሮ አዛሉ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ሲጠና ለውሃ መፋሰሻ ተገቢ የሆኑ ቦዮች ባለመሠራታቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጎርፍ እንዲያስቸግር አድርጓል፡፡ በመሆኑም ዘላቂ ሥራ ለመሥራት ኮርፖሬሽኑ በጥናት ላይ የተደገፈ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባል ዶክተር ኤዲያና ኃይለ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶች ከግዝፈታቸውና ከአዲስነታቸው አንጻር ሲታዩ አፈጻጸማቸው አበረታች ቢሆንም ከሚፈጥሩት አካባቢያዊ ተጽዕኖ አንጻር የተሄደበት ርቀት በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አዋሽ ፓርክ አካባቢ ቅድመ ጥንቃቄ ባለመደረጉ የዱር አራዊቶቹ ፓርኩን ጥለው እንዲኮበልሉና በተፈጠረው ክፍተት እንዲወጡ ያደረገ ሲሆን፤ እንስሳቶቹም በህገ ወጥ መንገድ ታድነው ለምግብነት እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በሚሆኑበት ወቅት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ዳባ ቱንካ፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሃሳብ ዲዛይን እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ለሁሉም ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጥናቶች ተደርገው የተቀመጡ መረጃዎች በኮርፖሬሽኑ አይገኙም፡፡ ይሁን እንጂ የፕሮጀክቶች አሠራር ከጥቅል ሃሳብ ተነስቶ ወደ ዝርዝር ሃሳብ የሚደረግ ትግበራ በመሆኑ መሬት ላይ ባለ እውነታ እንጂ በመረጃ መልኩ በተያዘው ሰነድ ብቻ ተግባራዊ ላይደረግ ስለሚችል ሰነዶች ባይኖሩም ለተግባራዊነቱ እንቅፋት አይፈጠርም ባይ ናቸው፡፡
የፕሮጀክቶች ውል ዲዛይን ሲዘጋጅ ተቋራጩ ሥራዎችን ከአካባቢ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ግንባታውን እያከናወነ ችግሮችን እያጠና እንዲሁም ችግር ከተፈጠረ እየፈታ የሚሄድበት ስምምነት በመሆኑ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ጥናት አያስፈልግም ይላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ውል «ዲዛይን ቢውልድ» ማለትም ተቋራጩ ሥራውን እያከናወነ ችግሮችን እያጠና የሚሠራበት ስምምነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ስምምነቱ «ዲዛይን ቢድ ቢውልድ» ቢሆን ኖሮ ተቋራጩ በተሰጠው የተጠና ጥናት መሠረት ምንም ሳይጨምርና ሳይቀንስ ጥናቱን ተግባራዊ የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይ ለሰዎች መተላለፊያ ቦታዎች ላይ ችግር እንዳለ የሚስተዋል በመሆኑ መፍትሔ እየተሰጠው የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራልም ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ሥራዎቹ በአብዛኛው በተቋራጩ ተጠያቂነት የሚሠሩ በመሆናቸው ዝርዝር ጥናት ላያስፈልግ ይችላል የሚሉት ኢንጅነር ዳባ፤ በተጣበበ ጊዜ በሦስት ዓመታት ውስጥ የተስተካከለ ፕላን በሌላት ከተማ ውስጥ ተግባራዊ መሆኑ በየትኛውም አጎራባች አገሮች ያልተደረገና በፍጥነት ለቁም ነገር የበቃ ፕሮጀክት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ቃሊቲ አካባቢ ከተሠራ በኋላ እንዲፈርስ የተደረገው ከሌሎች መሰረተ ልማት ጋር ለማስተሳሰር እንደሆነና ወለንጪቲ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ዱከምና ገላን ከተማ በተሠሩ የከባድ መኪና ማቋረጫ ቦታዎች ላይ የተሠራው ድልድይ ከፍታ 5 ነጥብ 4 ሜትር በስታንዳርድ መሰረት መሆኑን አስታውሰው፤ ከፍታ ያላቸው ጭነቶች ማለፍ አለመቻላቸው የስታንዳርዱ ችግር በመሆኑ በአካባቢዎች ተለዋጭ መንገዶችን መሥራት እንደሚጠበቅና ስታንዳርዱ የሚጨመርበት ሁኔታ ካለ የተሻለ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር ፕሮጀክት ግዙፍ ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን የአካባቢ ተጽዕኖን በሚመለከት የተፈጠሩ ችግሮች ከሥራው አኳያ ቀላል መሆናቸውን ተናግረው፤ አዋሽ ፓርክ አካባቢ የተፈጠረው የዱር እንስሳት መፈናቀልና አላግባብ መታደን መስተካከል የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ፀሐፊ ዑመር እንድሪስ
– See more at: http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/business-market/item/7527-2016-06-12-17-01-28#sthash.uAWnhrhi.IPz6Ecph.dpuf