አክሱም ጥቅምት 18/2006 በትግራይ ምእራባዊ ዞን አዲሐርሽና ማይአይኒ የተጠለሉ ጥቂት የኤርትራ ስደተኞች ያካሄዱትን ሕገወጥ ድርጊት በሽመልባ የተጠለሉ የኤርትራ ስደተኞች አወገዙ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስትንም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉምን ድንበሮች ክፍት በማድረግ ስደተኞችን ለመቀበል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያደንቅ በተባበሩት መንግስታት የስተደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩ ኤን ኤች ሲ አር/ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ መስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲሐርሽና ማይአይኒ ካምኘ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች በጣሊያን ላምፔዱሳ በጀልባ ጉዞ ላይ የነበሩትና የሰመጡትን ኤርትራውያን ስደተኞች ለመዘከር የጧፍ ማብራትና የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ይጠይቃሉ፡፡ ሆኖም ስደተኞቹ የጠየቁትን ፈቃድ በመጣስ የሻእቢያ ተላላኪዎችን በማሰባሰብ በእርዳታ ሰጪ ተቋማት ሠራተኞችና ድጋፍ ሰጪዎች ላይ ድንጋይ በመወርመር ያደረሱን ጉዳት በሽመልባ የሚኖሩ የኤርትራ ስደተኞች ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሰትም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በሽመልባ ካምኘ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ በማይአይኒና አዲሐርስ በጥቂት የሻእቢያ ተላላኪ አስባባሪነት የተካሄደውን ሕገወጥ ድርጊት እናወግዛለን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግስት ይቅርታ እንጠይቃለን፣ ሕገወጥ ሰልፉ እኛን የኤርትራ ስደተኞችን አይወክልም፣ የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አስተጋብተዋል፡፡ ከሰልፈኞቹ መካከል ለቱ ኡስማን፣ ወጣቶች ደጀን ናይእግዚ፣ ዩናስ ኃይለማርያም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት የተጠለልንባት ጐረቤታችን ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት የምትመራ እንደመሆኗ ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ችግሮቻችን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ሲገባን በጥቂት የሻእቢያ ተላላኪ ስደተኞች የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን የኤርትራ ስደተኞች እንደማይወክሉ ተናግረዋል፡፡ ”በአገራችን ሰላምና ዴሞክራሲ አጣን ብለን ተሰደን የተሻለ ሰላም የምናገኝባትን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሰላምና ልማት ማወክ ተገቢ አይደለም” ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በስደተኞችና በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የተፈጠረውን መግባባት እንዲጠናከር እንጥራለን ለተፈጠረው ችግርም ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የስተደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩ ኤን ኤች ሲ አር/ የሽሬ እንዳስላሴ የስደተኛ ህፃናት እንክብካቤ አስተባባሪ ራምሴ ብራዊት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ድንበሮች ክፍት በማድረግ ስደተኞቹን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከ400 ሺህ በላይ ከኤርትራ፣ ሶማሊያና ሱዳን የመጡ ስደተኞች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ 50 ሺህ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ENA
tweet