በተስፋሁን ብርሃኑ
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ገነት ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም ባለቤቴን እግሯን ሰብሯል በሚል የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበት ከማረሚያ ቤት የወጣውን ወንድሙን በዱላና በቦክስ በመምታት ለሞት ዳርጎታል የተባለው በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል መርማሪ የሆኑት ረ/ሳ አዲስ የወንጀል ድርጊቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት ሟች የተጠርጣሪን ሚስት እግሯን ሰብሮ የፍርድ ውሳኔ ተላልፎበት ዘጠኝ ወር ከታሰረ በኋላ ተፈትቷል። ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም ሟች ምትኩ ጫላ ከማረሚያ ቤት የወጣ ቀን ቤት ውስጥ ይገናኛሉ። ተጠርጣሪ የባለቤቴን እግር ሰብረህ እንዴት ቤት ትመጣለህ በማለት በዱላና በቦክስ ይደበድውና ከፍተኛ ጉዳት ያደርስበታል።
ሟች በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና ቢደረገለትም ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወቱ በዚያው ሊያልፍ እንደቻለ መርማሪው ነግረውናል። ፖሊስም ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል አስፈላጊውን የሰውና የህክምና ማስረጃዎችን በማጠናቀቅ ለዓቃቤ ህግ ልኮታል። የፌደራሉ ዐቃቤ ህግም የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ በማጠናከር ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመላክ ክስ እንዲመሰረትበት አድርጓል ሲሉ መርማሪው ነግረውናል።
ምንጭ: ፖሊስና ርምጃው





