Sunday , 25 December 2016

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 5 የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ – በቀለ ጉተማ የትምህርት ክፍል የፕሬፌሰርነት ማዕረግ በማግኘት የመጀመሪያው ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ ስራዎቻቸው በየትምህርት ክፍሎቻቸው ጉባዔዎች፣ በኮሌጆቹ የአካዳሚክ ኮሚሽኖች፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግመው የቀረቡለትን አምስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አጽድቋል፡፡

ከዚህ በታች ስለ ምሁራኑ ስራዎች አጭር መግለጫ ሰፍሯል፡፡

ኘሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ጋሞ ጐፋ ክፍለ ሀገር ተከታትለዋል፡፡ ኘሮፌሰር አድማሱ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በእጽዋት ሳይንስ ከቀድሞው አለማያ የእርሻ ኮሌጅ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በክሮፕ ኢኮሎጂ እና ሪሶርስ ኮንዘርቬሽን (Crop Ecology and Resource Conservation) ኒዘርላንድስ ከሚገኘው ዋግንገን ዩኒቨርሲቲ(Wageningen University) አግኝተዋል፡፡

ኘሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ በእንሰት እና በሥራሥር ተክሎች ላይ በርከት ያሉ ምርምሮችን በማከናወንና የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን በማማከር በታወቁ ጆርናሎች ላይ ከ31 በላይ ጽሁፎችን አሳትመዋል፡፡ በተለይ ብዙ የምርምር መረጃዎች በሌሉበት በእንሰት ተክል ላይ ስለ እንሰት አስተዳደግ፣ ሥነ-ምህዳር ምርታማነት፣ ሥነ-ምግብ፣ የብዝሃ-ህይወት ልዩነትና ሥርጭት በርካታ ምርምሮችን አከናውነዋል፡፡

በጥናታቸው የእንሰት ምርታማነት ከጊዜና ከሚይዘው ቦታ አንፃር ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲወዳደር ምርታማነቱ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን፣ ከእንሰት ተክል የሚሠሩ ምግቦች የምግብ ንጥረነገሮች ይዘት ከሌሎች የሥራሥር ተክሎች የማያንስ መሆኑንና በተለይም የእንሰት ምግቦች የብረትና ዚንክ (Fe and Zn) መጠን ከሌሎች ሥራሥር ተክሎች የበለጠ መሆኑን፣ በሀገራችን የእንሰት አብቃይ አካባቢዎች በአካባቢው ቋንቋ የተለያዩ ስሞች የሚሰጧቸው የእንሰት ዓይነቶች በአብዛኛው በዘረ-መል የተለያዩ በመሆናቸው ያሉዋቸው የምግብ ንጥረ-ነገሮች ኘሮቲን እና የመሳሰሉት መጠኖች በእጅጉ የሚለያዩ መሆኑን፣ በዝርያዎቹ ውስጥ ያሉት ጠቃሚና ጠቃሚ ያልሆኑ አሚኖ አሲድ(Amino Acids) መጠናቸው በጣም የሚለያይ መሆኑንና ይህም ወደፊት መረጣ በማከናወን የእንሰትን ተፈላጊነት በቀላሉ ማሳደግ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የድንች ተክል ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ገበያ ድረስ ያለውን የምርትና የግብይት ሥርዓት(value chain) በማጥናት የድንችን ተክል ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ መንገዶችን አሳይተዋል፡፡

ኘሮፌሰር አድማሱ ከምርምርና ከማስተማር ሥራቸው ጐንለጐን በቀድሞው የአዋሳ ግብርና ኮሌጅ የአስተዳደር ዲን፣ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ም/ኘሬዚዳንት፣ የአካዳሚክና ምርምር ም/ኘሬዚዳንት እና ኘሬዝዳንት በመሆን ካገለገሉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመዛወር ላለፉት አምስት ዓመታት በኘሬዚዳንትነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ኘሮፌሰር አድማሱ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋሙ የተለያዩ ቦርዶች በሰብሳቢነት፣ በምክትል ሰብሳቢነትና በአባልነት በማገልገል ለአገራችን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ ምሁር ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ አገልግሎታቸው በትምህርት ክፍላቸው ጉባዔ፣ በኮሌጁ የአካዳሚክ ኮሚሽን፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግሞ ለሥራ አመራር ቦርዱ በቀረበው መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በክሮፕ ኢኮሎጂ እና ሪሶርስ ኮንዘርቬሽን (Crop Ecology and Resource Conservation) የኘሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም ባደረግው ስብሳባ ወስኗል፡፡

ፕሮፌሰር መሀመድ አስን

ፕሮፌሰር መሀመድ አስን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ድግሪያቸውን በጂኦግራፊ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በአፈር ሳይንስ (Soil Science) ከፍሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ደቡብ አፍሪካ አግኝተዋል፡፡

ፕሬፌሰር መሀመድ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት እና በአማካሪነት ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አገልግለዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ እና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮች እንዲከፈቱ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀሉ ጀምሮ የጆኦግራፊ  ትምህርት ክፍልን በሀላፊነት በመምራት፣ በማስተማር፣ በመመራመር እና ተማሪዎችን በማማከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መሀመድ በማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ ከፍተኛ አስታዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ፕሬፌሰር መሀመድ አስን በሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ በጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ የምርምር ስራዎቻቸው የሚያተኩሩት በአፈር እና አካባቢ ሳይንስ፣ ሀይድሮሎጂ፣ በመሬት አጠቃቀምና ተፋሰስ ልማት ላይ ሲሆን እስካሁን ድረስ 40 ያህል የጥናት እና ምርምር ውጤቶች በታወቁ ሙያዊ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ አገልግሎታቸው በትምህርት ክፍላቸው ጉባዔ፣ በኮሌጁ የአካዳሚክ ኮሚሽን፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግሞ ለሥራ አመራር ቦርዱ በቀረበው መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በፔዶግራፊ እና ላንድ ኢቫሊዌሽን (Pedography and Land Evaluation) የኘሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም ባደረግው ስብሰባ ወስኗል፡፡

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ የመጀመሪየያ ድግሪያቸውን በፍልስፍና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በፍልስፍና ከጀርመን ፍሪድሪሽ ሽለር ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፍልስፍና ከኦስትሪያ  ቬይና ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ ከሰላሳ አመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል በማስተማር፣ በምርምር እና የሶሻል ሳይንስ ዲንነትን ጨምሮ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች አገልግለዋል፡፡

የፕሮፌሰር በቀለ የማስተማር እና ምርምር ትኩረት የአፍሪካ ፍልስፍና፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍልስፍና (Social and Political philosophy) እንዲሁም እንተርካልቸራል ፍልስፍና (Intercultural Philosophy) ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር በቀለ በእነዚህና ተዛማጅ መስኮች ከሀያ በላይ የምርምር ጽሑፎችን በታወቁ አለምአቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ በአመት ሁለት ጊዜ የሚታተመውን (Ethiopian Journal of the Social Sciences and Humanities) በማቋቋም፤ ዋና ኤዲተር (Editor-in-Chief) በመሆንና በመምራት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በየአምስት አመቱ የሚካሄደውን የአለም ፍልስፍና ኮንግረንስ ጨምሮ በበርካታ አገራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ አገልግሎታቸው በትምህርት ክፍላቸው ጉባዔ፣ በኮሌጁ የአካዳሚክ ኮሚሽን፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግሞ ለሥራ አመራር ቦርዱ በቀረበው መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በፍልስፍና (Philosophy) የኘሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም ባደረግው ስብሰባ ወስኗል፡፡

ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የፕሬፌሰርነት ማዕረግ በማግኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ጀማል ሀይደር

ፕሮፌሰር ጀማል ሃይደር የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በህክምና ዶክትሬት ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ከተቀበሉ በኋላ በሂውማን ኑትሪሸንና በማይክሮኑትሪየንት (ጥቃቅንና ንጥረምግቦች) በናይሮቢና ደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጀማል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በሀኪምነት፣ በሆስፒታል ሃላፊነት፣ በክልል ስራ አስኪየጅነት፣ በፕሮግራም አስተባባሪነት፤ በመምህርነትና በምርምር እንዲሁም የኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክትር ጄንራል በመሆን ለ 20 አመታት  በጤና ጥበቃ ስር በሚገኙ ተቋማት ሲያገለግሉ የተለያዩ የኑትረሽን መርጃዎችን፣ የህፃናት አመጋገብ ማኑዋሎችና መፃፎችን ጽፈዋል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው በህብረተሰብ ጤና ት/ቤት በመምህርነት፤ በትምህርት ክፍል እና በትምህርት ቤት ሃላፊነት በተለያዩ ግዜያት ያገለገሉ ሲሆን ከ 80 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በተለያዩ  የአለም አቀፍና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ላበረከቱት የማሰተማርና የምርምር አስተዋጽኦ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎችም ሸልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ አገልግሎታቸው በትምህርት ክፍላቸው ጉባዔ፣ በኮሌጁ የአካዳሚክ ኮሚሽን፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግሞ ለሥራ አመራር ቦርዱ በቀረበው መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በማህበረሰብ ጤና (Public Health) የኘሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም ባደረግው ስብሰባ ወስኗል፡፡

ፕሮፌሰር አስፋው አጥናፉ

ፕሮፌሰር አስፋው አጥናፉ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በህክምና ዶክትሬት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሬዲዮሎጂስት ስፔሻሊቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ፣ ተጨማሪ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሄልዝ ኢንፎርማቲክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ ድግሪያቸውን በቦዲ ኢማጂንግ (Body Imaging) ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትብብር አግኝተዋል፡፡

ፕሬፌሰር አስፋው አጥናፉ ሬዲዮሎጂስትና የቦዲ ኢሜጂንግ ሰብ ስፔሻሊስት ሲሆኑ በሙያቸው ከሃያ አምስት ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ በህክምና ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት የryዲዮሎጂ ትምህርት ክፍሉን ከመሰረቱት አንጋፋ ራዲዮሎጂስቶች አንዱ ሲሆኑ እስከ አሁንም በማስተማር ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማድረግ በአገር ውስጥና ውጪ ባሉ የምርምር ጆርናሎች ከሃያ ሰባት በላይ የምርምር ውጤቶችን ለሕትመት አብቅተዋል፡፡ የፕሮፌሰር አስፋው የምርምር አቅጣጫ ያተኮረው የተለያዩ የበሽታ አይነቶች (ቲቢ፣ ሊንፎማና የመሳሰሉ) የሬዲዮሎጂ መገለጫዎችን በሚመለከት ሲሆን በተጨማሪም ለህመምተኞች እና የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች በሬዲዮሎጂ አጠቃቀም ሊከተሉት የሚገባውን አካሄድ በማስመልከት በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሬድዮሎጂ ሙያ ደረጃና ለወደፊት ሙያውን ለማሻሻል ሊደረጉ የሚገባቸውን አቅጣጫዎችና ብሎም ከአገር ውጪ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የአገልግሎቱንና የማስተማር ሂደት በምን መልክ መስፋፋት እና ማደግ እንደሚገባው በጥናታቸው አሳይተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አስፋው ባላቸው ተጨማሪና ተጓዳኝነት ባለው ICT ጋር በተያያዘ ሙያቸው ሬዲዮሎጂንና በአጠቃላይ የቴሌሜድስን አገልግሎት በኢትዮጵያ እና በመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች የባለሙያዎችን እጥረት በማካካስ የህክምና ጥራትን ለማሻሻል እንደሚረዳና የአገሪቱን ሪፈራል መርሃ ግብር በምን መልክ መደገፍ እንደሚችል በምርምር ጽሁፋቸው አሳይተዋል፡፡

ፕሬፌሰር አስፋው የሞባይል ስልክ ቴክኖሎጂ በጤና አገልግሎት ላይ በአገራችን ሊኖረው የሚችለውን ከፍተኛ ሚና በተለይም የእናቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ በሚያስችልበት መልኩ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሙከራ ለማድረግ የቴክኒዎሎጂውን ጠቀሜታ በማሳየት ስድስት የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመዋል፡፡

በአጠቃላይ ፕሬፌሰር አስፋው ባለፉት ሃያ አምስት አመታት ለአገሪቱ የሕክምና አገልግሎት፣ መማር ማስተማርና ምርምር ላይ በተለይም በሬዲዮሎጂ ሙያ መስፋፋት እና ጥራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ህግ በሚያዘው መሠረት የምርምር፣ የማስተማርና የማኀበረሰብ አገልግሎታቸው በትምህርት ክፍላቸው ጉባዔ፣ በኮሌጁ የአካዳሚክ ኮሚሽን፣ በተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን እና በሴኔት ተገምግሞ ለሥራ አመራር ቦርዱ በቀረበው መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በሬዲዮሎጂ (Radiology) የኘሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ታህሳስ 12/2009 ዓ.ም ባደረግው ስብሰባ ወስኗል፡፡

source: ena

 

Leave a Reply