አዲስ አበባ ነሃሴ 19/2008 የ2009 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ይፋ ሆነ።
የመግቢያ ውጤቱን ይፋ ያደረጉት የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሳ ናቸው።
በዚህም መሠረት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡት ሁሉም መደበኛና የማታ ተማሪዎች ወንዶች 354 እና በላይ ሴቶች 340 እና በላይ ውጤት ያመጡ ይሆናሉ።
ለግል ተፈታኞች ደግሞ ወንዶች 360 እና በላይ፣ሴቶች 355 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ልዩ ድጋፍ በሚሹና ታዳጊና አርብቶ አደር አካባቢ ተማሪዎች ደግሞ ለወንዶች 340 እና ለሴቶች 335 እና ከዚያ በላይ እንዲሆን ተወስኗል።
መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች በሁለቱም ጾታ 297 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ወደ መንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባሉ።
በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ደግሞ ሁሉም መደበኛና የማታ ተማሪዎች ለወንዶች 330 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴቶች 320 እና ከዚያ በላይ ሆኗል።
የግል ተፈታኝ ወንዶች 360 እና በላይ ሴቶች 355 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን መከታተል ይችላሉ።
ለታዳጊና የአርብቶ አደር አካባቢ ተማሪዎች ደግሞ ወንዶች 320 እና በላይ ሲሆን ለሴቶች 315 እና በላይ ሆኗል።
መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ለሁለቱም ጾታ 275 እና በላይ ሲሆን ማየት የተሳናቸው ወንዶችና ሴቶች ደግሞ 200 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይመደባሉ ተብሏል።
ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 2 ሺህ 150 ተማሪዎች በህክምና ትምህርት ገብተው እንዲማሩ መወሰኑንም ምክትል ዳሬክተሩ ተናግረዋ።
በነጥቡ መሰረት ተማሪዎች ምርጫቸውን እንዲያስተካክሉና የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችም እንዲያስተናግዱ አሳስበዋል።
በ2009 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ አጠቃላይ 185 ሺህ 772 ተማሪዎች ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ በ136 ሺህ 322 በመንግስት እንዲሁም 50 ሺህ ተማሪዎች በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ይሆናል።
በዘንድሮው ዓመት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው የሚማሩት ተማሪዎች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ10 በመቶ ጨምሯል።
የሴቶች ተሳትፎም ባለፈው ዓመት ከነበረው 39 በመቶ ወደ 42 ነጥብ 5 አድጓል።
Source: ENA
