በጫት፣ ልብስና መጫሚያ፣ የማገዶ እንጨት፣ የቤት ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታየ

0
517

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009 የመጋቢት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው ንዳስታወቀው፤ የመጋቢት አጠቃላይ ግሽበት 8 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህም ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በሁለት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያመለክታል።

በተያዘው ወር በእህል ክፍሎች በተለይም በበቆሎ ላይ ጭማሪ የታየ ሲሆን፤ በአትክልት ላይ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።

የጥራጥሬ፣ ድንች፣ ቆጮና ቡና ዋጋዎች ላይም በተመሳሳይ ጭማሪ ታይቷል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ መመዝገቡን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በጫት፣ ልብስና መጫሚያ፣ የማገዶ እንጨት፣ የቤት ዕቃዎችና ማስጌጫዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ለአጠቃላይ ዋጋ ግሽበቱ መጨመር ምክንያት መሆኑንም ጠቅሷል።

በዚህ በኩል በአማራ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልሎች ፈጣን የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነው ኤጀንሲው የገለጸው።

Source: ENA