በአዲስ አበባ በቦሌ የታክሲ ሹፌሩን የገደለው ምርመራ እየተጣራበት ነው

0
364

በተስፋሁን ብርሃኑ

Feb. 21, 2014

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ስሙ ዘርፈ ሸዋን ትምህርት ቤት አካባቢ ቤተሰቦቹን ጭኖ ሲጓዝ የነበረውን ሟች ወንደሰን ደምሴን የገደለው ምርመራ እየተጣራበት እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ የወንጀል ድርጊቱ መርማሪ የሆኑት ም/ሳጅን ግሩም ታረቀኝ እንደተናገሩት ሟች ወንደሰን ደምሴ ታህሳስ 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ የአባቱ ንብረት የሆነችውን የህዝብ ማመላለሻ መኪና በመያዝ ቤተሰቦቹን ጭኖ ይጓዛል፡፡ ተጠርጣሪው ደጀኔ ገመቹ የተባለው መኪናውን ካስቆመ በኋላ ንዲያሳፍረው ይጠይቀዋል፡፡ መጀመሪያ ከመኪናው ረዳት ጋር ‹‹አሳፍረኝ አላሳፍርም›› በሚል ፀብ ይፈጥራሉ፡፡ በኋላም ሹፌሩ መሀል በመግባት ፀቡን ለማብረድ ቤተሰቡን ይዞ እየሄደ እንደሆነና ማንንም ተሳፋሪ እንደማይጭን ለተጠርጣሪው ይነግረዋል፡፡ ተጠርጣሪውም ፀቡን ከማብረድና ሌላ አማራጭ ከመፈለግ ይልቅ ‹‹አታሳፍሩኝም›› በማለት በያዘው ሽጉጥ አሽከርካሪውን አንገቱ ላይ ተኩሶ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ እንዳደረገ በምርመራው የተገኘውን ማስረጃ በመጥቀስ መርማሪው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ፖሊስም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ካጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ ልኮ ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል›› ሲሉ መርማሪው ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት እንደዚህ አይነት ቀላልና ጊዜያዊ ግጭቶችን በሰላምና በመቻቻል ማሳለፍ ሲገባ የሰው ህይወት መጥፋቱ ተገቢ እንዳልሆነና ህብረተሰቡ የመቻቻልና ግጭቶችን በውይይት የመፍታት ባህሉን ሊያዳብር ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምንጭ: ፖሊስና ርምጃው 

[Google]